“ያለሴቶች ተሳትፎ ዴሞክራሲ የማይቻል ነው። እድገትም ያለዴሞክራሲ የማይታሰብ ነው።” ማደሊን ኬ አልብራይት
በራዕይ ኢትዮጵያ ፯ኛ ጉባዔ ላይ አዲስ አበባ የቀርበ
ታህሣሥ 18 ቀን 2011/ December 27, 2018
በወሰንየለሽ ደበላ
መነሻ ሀሳብ
ለአንድ አገር ብልፅግና የሀገሪቱ መረጋጋትና ሰላም መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ሰላም ማለት ስጋትና ፍርሃት የሌለበት፣ ጦርነት የማይካሄድበት፣ ግጭትና ሁከት የማይፈጠርበት፣ አለመረጋጋት፣ ጭቆና፣ ማስፈራራት፣ ጥቃት፣ ስድብ፣ አድልዎ የሌለበት ማለት ነው። ሰላም ምንም እንኳን የአመፅ አለመኖር ቢሆንም አወንታዊ ሰላም ግን በሰላማዊ ህዝቦች የሚንጸባርቅና ዘላቂ የሆኑትን ዝናባሌዎችን፣ መዋቅሮችንና ተቋሞች የሚገለፁበት ነው። የሰላም ድባብ መኖር ለእድገትና ለልማት አስፈላጊ መሠረት ነው። በለውጥ ላይ ያለ ሀገር የመጀመሪያ እንቅፋት የሚሆንበት የሰላም መደፍረስ ነው።
ሰላም ሲደፈርስ ገበሬ አርሶ መብላት፣ ነጋዴ ነግዶ መግባት፣ ልጆች ተጫውተው፣ ወጣቶች ተምረው፣ ከብቶች ተሰማርተው በሰላም መግባት አይችሉም። ማሕበረሰቡ በሰላም ወጥቶ ካልገባ ሀገር በህውከት ውስጥ ካለ መንግሥት ተረጋግቶ ሀገሪቱን ማስተዳደር አይችልም። ሰላም ከሌለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ የፖለቲካ መረጋጋትና የማህበራዊ ብልፅግና የማይታሰቡ ናቸው። ሰላም ከሌለ ሕዝብ ለከፋ ድህነትና በሽታ የተጋለጠ ይሆናሉ። ለምሳሌ እንደ ኤድስ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ በመራባት ትውልድን እምሽክ ያረጋሉ።