አክሎግ ቢራራ (ዶር)
የእርስ በእርስ ጦርነት ዛሬ አልተጀመረም።
የወልቃይት ጠገዴ፤ የጠለምት፤ የዋልድባ፤ የሰቲት ሁመራ፤ የራያና አዜቦ፤ የትግራይ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ። ሊወገድ የሚችል ጦርነት መካሄዱ አሳፍሮኛል። ሊካድ የማይችለው ሃቅ ግን የዐማራው ሕዝብ በሽብርተኛው ብድህወሓትና በኦነግ ሽኔ ተከታታይ እልቂት ሲካሄድበት ቆይቷል። ህወሓት ባወጣው ማኒፌስቶ (መመሪያ) የፋሽስቱን የጣልያን ግፍ፤ በደልና የበላይነት ተመሳሳይ ነው በማለት “የዐማራው ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ዋናው ጠላት ነው” ብሎ ፈርዶበታል። ይህንን ትርክት ሌሎች የብሄር ጽንፈኞችና እንደ ኦነግ ሽኔ ያሉ ሽብርተኞች መሳሪያ አድርገው ዐማራውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዩን ጨፍጭፈውበታል። ይፋ አይሁን እንጅ ዐማራውን ኢላማ ያደረገ ያልታወጀ ጦርነት ሲካሄድ ከአርባ ዓመታት በላይ ሆኖታል።
ህወሓት የቀሰቀሰውን ጦርነት ጀግናው የመከላከያ ኃይል፤ ከነዋሪው ገበሬ፤ ከፋኖው፤ ከሚሊሺያውና ከሌላው አጋር ኃይል ጋር ሆኖ የሚያካሂደውን የጸረ- አመጸኞች ወይንም ሽብርተኞች፤ በተለይ ጸረ-ሰላም፤ እርጋታና ጸረ-ከሃዲነት እንቅስቃሴ አደንቃለሁ።
ይህ አላስፈላጊ ጦርነት የተጀመረው በህወሓት፤ በኦነግ ሽኔ፤ በጅሃዲስቶችና ከጀርባ ከፍተኛ ድጋፍ በሚሰጡ ኃይሎች፤ በተለይ በግብፅ መሆኑን በተከታታይ ትንተናዎቸ አሳስቤ ነበር። ኢትዮጵያን እኛ ካልገዛናትና ካልመዘበርናት የደም መሬት አድርገናት ትበተን የሚሉት ህወሓትና አጋሩ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ወታደራዊ ኃይል (The Oromo Liberation Army/OLA) ያመጡት ጠንቅ ነው።
ወረተኛ ካልሆንን በስተቀር ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና እርጋታ ያገኘው መቸ ነው? እኔ ወጣት ከአባቴ ጋር በበቁሎው ተሳፍሬ፤ እንዳልወድቅ ወገቡን ይዠ በያካባቢው ለሰርግ፤ ለለቅሶ፤ ለልዩ ልዩ በዓል ስንዞር አንድ ሰው ሌላውን “በሕግ አምላክ” ሲለው ካለበት የማይንቀሳቀስባት አገር ነበረች–እትዮጵያ።