ከመግባባትን ገንቢ የኢትዮጵያ መድረክ(መገኢመ)

ቀን፡ጥቅምት ፱፣ ፳፻፱ አ. ም.

ለመድረክ ጽ/ቤት

ከመግባባትን ገንቢ የኢትዮጵያ መድረክ(መገኢመ)
ዋሽንግቶን ዲሲ
አሜሪካ

ጉዳዩ፡ መ ገኢመን ስለማስተዋወቅና በኢትዮጵያ ዉስጥ ባሉ በተለያዩ የፖለቲካ አማራጭ ሀይሎችና በመንግሰት
መካከል ሀገራዊ ውይይት ( National dialogue) ማስጀመርን ይመለከታል፡፡

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታን እያቀረብን፣ ከወዲሁ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መረጋጋትን ብሎም
ብልጽግናናን እንዲሰጥልን የጠበቀ ምኞታችንንና ጽኑ ፍላጎታችንን እንገልጻለን። በመቀጠልም የመገኢመን አላማና
ማንንታችን በጥቂቱ ከዚህ በታች አንገልጻለን።

መግባባትን ገንቢ የኢትዮጵያ መድረክ (መገኢመ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ፍትህ ዴሞክራሲና ልማት እንዲዳብር
ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብና በማወያየት በመካከላቸዉ መግባባትና መቻቻል እንዲኖር ለማድረግ በሚል መርህ
ተመርኩዞ እ.አ. አ. 2014 ዓ.ም. የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በአሰራሩም ባህላዊና ዘመናዊ የሽምግልና

ልምድና መሠረተ ሀሳቦችን እያቀናጀ በሀገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት በሚያስችል መንገድ አገናዝቦ በሥራ ላይ
ለማዋል ጥረት የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ መስራች አባላቱም ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ከቡድን ወገኝተኝነት፣
ከውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላትና ከአድሎ ነፃ ሆነው ለዘላቂ ሰላምና እድገት የቆሙ ከተለያዩ የሀገሪቱ ሕብረሕዝብ
ክፍሎች የታቀፉ፥ የተለያዩ የትምህርትና የስራ ልምድ ያላቸው ናቸው።

መገኢመ ይህንን ዓላማውን በሚገባ ለመወጣት ራሱን በሶስት አካላት አዋቅሮ ሥራ ጀምሯል። እነዚህም ከዚህ በታች
የተጠቀሱት ናቸው፦

(1) የአማራጭ ሀይሎችን የሚያነጋግር አካል፥ ሁሉም የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አማራጭ ሃይሎች እርስ
በርስ የሚያደርጉትን መቃቃርና መጠላለፍ ወደ ጎን በመተው የሀገራችንና የሕዝባችንን
የፖለቲካ ችግሮች ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ለመፍታትና ፈር ለማስያዝ የሚያስችሉ አማራጮችን
የሚያፈልቁና አማራጮቻቸዉን ቢቻል በአንድ ድምፅ ካልሆነም ደግሞ
እንደየፖሊሲዎቻቸዉና ፕሮግራሞቻቸዉ ተጣምረዉ ከመንግስትም ጋር የሰለጠነ ዉይይት
በማድረግ በሀገራችን የፖለቲካ መስክ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያድርጉ ለማወያየትና ለማግባባት
የሚጥር አካል ነው።

(2) መንግስትን የሚ ያነጋግር አካል፥ ይህ አካል መንግስት በውይይትና በመቻቻል ዘላቂ መፍትሄዎችን
በሕዝቡና በአማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ ተሳታፊነት ሊፈጠር የሚችል አማራጭ
የሌለው ሂደት መሆኑን እንዲገነዘብና ብሎም ከነዚህ አካላት ጋር ሊሰራ የሚችልበትን
መንገድ እንዲያመቻች ለማግባባት የሚጥር አካል ነው ። ይህም አካል መገኢመን
በነደፈው መመሪያ መሰረት ድርጅቱን ወክሎ ሥራውን የሚያከናውነው የመንግስት
ተቀባይነት ካላቸው ባገር ከሚኖሩ ሽማግሌዎችና ያገባናል ከሚ ሉ የአስታራቂና የአስተባባሪ
መንፈስ ከሚያሳዩ ወገኖች ጋር በመተባበርና በማስተባበር ነው።

(3) የትምህርት አደራጅ አካል፥ የሀገራችን ሕዝቦች በጥናትና እውነትን በመፈለግ ሥርዓት ላይ
የተመሰረተ እውቀትንና ጥበብን ተጎናፅፈው በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሁም

ለዲሞክራሲ ለፍትህና ለእኩልነት በሚደረገው ጥረት ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ
የሚያስችሉ ትምህርቶችን የሚያዘጋጅና የሚያወያይ አካል ነው። ይህ አካል ለዛሬይቱ
ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የነገዋም ኢትዮጵያ የፖለቲካና የአስተዳደር ችግሮች ሲገጥሟት
የሚከሰቱትን ችግሮች በሰላምና በውይይት የመፍታት የማስታረቅ ባህል እንዲዳብር
አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ የሚሞክርና ቀጣይ የሆነ መድረክ እንዲኖር የሚጥር
አካል ነው።

በአሁኑ ወቅት መገኢመ ከላይ የተጠቀሰውን መጠነ ሰፊ የሆነ የሽምግልና ስራ ለመስራት መኖሪያቸውን በኢትዮጵያ
ውስጥ አድርገዉ ተዛማጅ ሥራ እየሰሩ ካሉት የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አብሮ ለመስራት
እየተንቀሳቀስ ይገኛል። ድርጅቱ ከምንም ያልተወገነ ነጻ ሕልውናው እንደተጠበቀ ሆኖ፥ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ
ዲሞክራሲን፤ ሰላምን፤ ህብረትን፤ እኩልነትን፤ የሕግ የበላይነትና እድገትን ለማምጣት ከሚጥሩ አካላት ጋራ
ይተባበራል፡፡

አደረጃጀታችንና አላማችን ባጭሩ ከላይ እንደተገለጸዉ ሲሆን ይህንን ደብዳቤ ለመፃፍ ያነሳሳን ሀገራችን አሁን
ያለችበት ዉስጣዊና አካባቢያዊ አደገኛ ሁኔታ የፈጠረብን ጥልቅ ስጋት ነው። ከዚህም በመነሳት ይህ አደገኛ ሁኔታ
ካስከተላቸው በግብታዊነት ከሚደረጉ ጊዜያዊ የመፍትሄ ሙከራዎቸ ባሻገር ሀገሪቱን በዘላቂነት ለማረጋጋት
የሚያስችሉትን ስርነቀል እርምጃዎችን ለመዉሰድ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አምነናል።
እነዚህም፦ (1) መንግስት እነዚህን መሠረታዊ የመፍትሔ ሃሰቦች ለመተግበር ፈቃደኝነቱንና ቁርጠኝነቱን
እንዲያሳይና ተጨባጭ እርምጃዎችን መዉሰድ እንዲጃምር ለማበረታታትና ለማሳለጥ (2) መንግስት በየትኛዉም
መልኩ ችግሩን ብቻዉን ሊወጣዉ እንደማይችል ተረድቶ ከአማራጭ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር የሀገሪቱ ነባራዊ ችግሮችና
ዘላቂ መፍትሄዎችን በሚመለከት ሀገራዊ ዉይይትና መግባባት ሊያደርግ የሚችልበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት፤ (3)
እንዲሁም ሀገሪቱ ካለችበት ፈርጀ ብዙ ችግሮች መንጭቆ በማዉጣት ረገድ አማራጭ የፖለቲካ ሀይሎች ሊጫወቱ
የሚችሉትን አይነተኛ ሚና ማበርከት እነዲችሉ ሁነኛ የፖለቲካና ማህበራዊ ምህዳር እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታ መፍጠር
ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ለአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና ህዝብ ድምጹን በስርዓት ማሰማት ስለአለመቻሉ
መንግስትም ሆነ አማራጭ ሀይሎች በየደረጃቸዉ የሚነቀፉባቸው ነጥቦች መኖራቸውን ብናምንም ድርጅታችን ሊጫወት
ከሚያስበዉ አይነተኛ የማግባባትና የሽምግልና ሚና አንጻር ማንንም ከመንቀፍና ከመፈረጅ ተቆጥበን በገለልተኝነት

ሁሉንም የሚመለከታቸዉን ወገኖች በማነጋገርና በመሸምገል ውጤታማ ወደሆነ ሀገራዊ ዉይይትና መግባባት
እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለን፡፡

ሁሉም እደሚረዳዉ በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የምንሰማዉ የህዝብ ቁጣና ይኸንኑ ተከትሎ የተፈጠሩ
አለመረጋጋቶች መነሻቸዉ ምንም ይሁን ምን ህዝብ የሚወክሉትና ድምጹን የሚያሰሙለት አማራጭ የፖለቲካ
ድርጅቶች በየደረጃዉ ባሉ የሕዝብ አስተዳደር መዋቅሮችም ውስጥ ይሁን የሕዝብ ምክርቤቶች ውስጥ ጭራሽ
ካአለመኖራቸዉ ባሻገር ያሉትም ድርጅቶች ቢሆኑ እርስ በርስ ከመጠላለፍና ከመበታተን አልፈዉ ህዝብ ተስፋ
የሚጥልባቸዉ ሆነዉ አለመገኘታቸዉ የዲሞክራሲ ስርዓቱን ከማቀጨጩም በላይ ዜጎች “ድምጻችንን የሚያሰማልን
የፖላቲካ ሀይል የለንም” ብለዉ ተስፋ በመቁረጥ በሚወስዱት ግብታዊ የሆኑ “መሪ አልባ” እርምጃዎች ሀገሪቱ
ወደአለመረጋገት እንዳታመራ በብርቱ የሚያሰጋ ስለሆነ ጭምር ነዉ፡፡ ይኸንን ሁኔታ ሁሉም የሚገነዘበው ስለሚሆን
የሕዝብን ድምጽ የሚወክሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ብሎም የፖለቲካ መሪዎች አልባነት የሚያስከትለውን አደጋ
መገመት ብዙ ትንተናና ዘገባ የሚያስፈልገው አይመስለንም። ስለሆነም አማራጭ የፖለቲካ ሐይሎች የህዝብን
ሀሳቦች፤ጥያቄዎችንና ብሶቶችን በማሰባሰብና በማስተባበር ብሎም በሚወክሉት ህዝብ ስም ከመንግሰትጋር መወያየት
መቻል መተኪያ የሌለዉ አይነተኛ የስራ ድርሻቸዉ ነዉ ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም አማራጭ የፖለቲካ ሐይሎች
አማራጮቻቸዉን ቢቻል በአንድ ድምፅ ከልሆነም ደግሞ እንደየፖሊሲዎቻቸዉና ፕሮግራሞቻቸዉ ተዛማጅነት
ተጣምረዉ ከመንግስትም ጋር የሰለጠነ ዉይይት በማድረግ የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ሂደት ወደፊት እንዲያራምዱ
ለማስቻል ድርጅታችን ባንድ ወገን አማራጭ የፖለቲካ ሐይሎችን ከመንግስት ጋር እንዲነጋገሩ፤በሌላ በኩል ደግሞ
እኒሁ ኃይሎች እርስ በርሳቸዉ ዉይይት እንዲያደርጉ ለማስተባበርና ለማሳለጥ ዝግጁዎች ነን፡፡

ይህን ስራችንን ስንጀምር አንዳንድ አካላት ድርጅታችን“አማራጭ ሃይሎቸን ከፖለቲካ ትግላቸዉ በማዘናገት
የኢህአዴግን የፖለቲካ የበላይነትና እድሜ የማራዘም“ ወይም በተቃራኒዉ ኢህአዴግን ከሚቀጥለዉ ምርጫ በፊት
በአቋራጭ በማፍረስ ሌላ መንግስት የማቋቋም አጀንዳ አለዉ”የሚሉ መላ ምቶችን በመሰንዘር ሊፈጥሩ በሚችሉት
የፖለቲካ መጠራጠሮችና መጠላለፎች ምክንያት ስራችንና ዓላማችን ተደናቅፎ እንዳይቀር ብንሰጋም ጥረታችን
ለሀገራችንና ለህዝባችን ካለን ፍቅርና መልካም አሳቢነት መሆኑን ሁሉም ተረድቶልን የምናስጀምረዉ ቅዱስ አላማ
ያለውን አገራዊ ዉይይት ጥቃቅን በሆኑ በስነስርአታዊ ጉዳዮች፤ ወይም በቅድመ ሁኔታዎችና በድብቅ ፍላጎቶች
እንዳይሰናከል ተሳታፊዎች የሚያስፈልገውን ሁሉ ሀገራዊና ሕዝባዊ ትብብር እንደሚያደርጉልን ጽኑ ተስፋ አለን፡፡

ለዚህም ዓይነት ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ብለን ተስፋ የጣልንበት ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ያለ ምንም ወገንተኛነትና
አድልዎ በሌለበት አካሄድ ከላይ በገለጽነዉ ሁኔታ ሀገራዊ ዉይይትና መግባባት አንዲጀመር ለማሳላጥ ያለንን ሙሉ
ቁርጠኝነት ለመግለጽ እንወዳለን።

በአጭሩ ከላይ በጥቅሉ የገለጽናቸዉን ሀሳቦች ብሎም ሀገሪቱ ያለችበትን አጣዳፊ ሁኔታ ግምት ዉስጥ በማስገባት
በመንግስትና በአማራጭ የፖለቲካ ሃይሎቸ መካከል አጠቃላይ ሀገራዊ ዉይይትና መግባባት እንዲኖር የጀመርነውን
ጥረት እያካሄድን፣ እንዲሁም ጎን ለጎን አማራጭ የፖለቲካ ሀይሎችን በአስቸኳይ እርስ በርስ የሚግባቡበትን የጋራ
የጎንዮሽ ሁነኛ ዉይይት ማስጀመር እንድንችል ድርጅትዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዉን ዝግጁነት በአስቸኳይ
እንዲገልጽልን በትህትና እጠይቃልን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።

ከሰላምታ ጋር

ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግሥቱ፤ ዋና አስተባባሪ
ከመግባባትን ገንቢ የኢትዮጵያ መድረክ(መገኢመ)
ዋሽንግቶን ዲሲ
አሜሪካ

To  Read More Please Click Here

Share: