መግባባትን ገንቢ የኢትዮጵያ መድረክ (Ethiopian Forum for Constructive
Engagement) ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ዋና መስሪያ ቤቱ ዋሺንግተን ዲሲ ሲሆን “በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ፍትህ
ዴሞክራሲና ልማት እንዲዳብር ባለድርሻ አካላትን ማቀራረብና መግባባት እንዲኖር” ለማመቻቸትና “ባህላዊና
ዘመናዊ በሆነ የሽምግልና አሰራር በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት፣ መወያየትና መቻቻል እንዲኖር
ጥረት” ለማድረግ እ.አ. አ. 2014 የተቋቋመ ድርጅት ነው። በባህላዊና በዘመናዊ የሽምግልና ልምድ መሠረት
የተቋቋመ፣ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ከቡድን ወገኝተኝነት፣ ከውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላትና ከአድሎ ነፃ ሆነው ለዘላቂ
ሰላምና እድገት ዓላማ የቆሙ የተለያየ ሕብረ ሕዝብ ያቀፈ፥ በተለያዩ የትምህርትና የስራ ልምምድ ያላቸው አካል
ነው።
ይህንን ዓላማውን በሚገባ ለመወጣትና ለማሟላት ድርጅታችን ለየት ያለ አወቃቀርና ሂደት መከተል አስፈላጊ
መሆኑን በመገንዘብ ራሳችንን በሶስት አካላት አዋቅረናል። እነዚህም ሶስቱ አካላት፥
(1) መንግስትን የሚያነጋግር አካል፥ መንግስት በውይይትና በመቻቻል ዘላቂ መፍትሄዎችን በሕዝቡና
በአማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ ተሳታፊነት መሻት አማራጭ የሌለው ሂደት መሆኑን
ማግባባትና ወደ ውይይቱ ጎዳና ለማምጣት የሚጥር አካል ነው። ይህም አካል የሚሰራው
በግለኝነት ሳይሆን የመንግስት ተቀባይነት ባላቸው ባገር ከሚኖሩ ሽማግሌዎችና ያገባናል
ከሚሉ የአስታራቂና የአስተባባሪ መንፈስ ከሚያሳዩ ወገኖች በመተባበር ነው።
(2) የአማራጭ ሀይሎችን የሚያነጋግር አካል፥ ሁሉም የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አማራጭ ሃይሎች እርስ
በርስ የሚያደርጉትን መቃቃርና መጠላለፍ ወደ ጎን አድርገው የሀገራችንና የሕዝባችንን
የፖለቲካ ችግሮች ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ለመፍታትና ፈር ለማስያዝ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን
ለመፍጠርና ከመንግስት ጋር በአንድ ድምፅ ለመወያየትና በሀገራችን የፖለቲካ መስክ ሙሉ
ተሳትፎ እንዲያድርጉ የሚያስችላቸው ጊዜያዊ ወይንም ቋሚ የሆነ የአንድነት መድረክ
እንዲፈጥሩ ለማወያየትና ለማግባባት የሚጥር አካል ነው።
(3) የትምህርት አደራጅ አካል፥ የሀገራችን ሕዝቦች በጥናትና በእውነት ላይ የተመሰረተ እውቀት
ተጎናፅፈው በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ለዲሞክራሲ ለፍትህና ለእኩልነት
በሚደረገው ጥረት ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ትምህርቶችን የሚያዘጋጅና
የሚያወያይ አካል ነው። ይህ አካል ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የነገዋም ኢትዮጵያ
የፖለቲካ የአስተዳደር ችግሮች በገጠማት ቁጥር የተከሰቱትን ችግሮች በሰላም በውይይት
የመፍታት የማስታረቅ ባህላችን እንዲሆን ቀጣይ የሆነ መድረክ ነው።
ይህንን ደብዳቤ በአሁኑ ጊዜ ለመፃፍ ያነሳሱን ሁለት ምክንያቶች ናቸው። የመጀመሪያው በወቅቱ በአገራችን
እየሆነ ያለውን በሁሉም ወገኖቻችን ላይ ሲካሄድ የምናየውና የምንሰማው ሞት መንገላታት መታሰር መፈናቀልና
የሀብት መውደም እጅግ ስላሳዘነን፤ በመወሰድ ላይ ያሉት የመንግስት እርምጃዎች ቋሚና ዘላቂ መፍትሔ ያመጣሉ
ብለን ስላላመንበት፤ በሀገራችን በታሪኳ ደርሶባት የማታውቀው አደጋ ያንዣበበባት መስሎ ስለታየን ነው። ስለሆነም
ከሁሉ አስቀድመን በዋናነት በሽምግልና አቀራረብ እንደምናየው፥ መንግስት ሀገሪቱን ለማረጋጋትና ዘላቂ
መፍትሔዎችን ለመሻት አማራጭ የሌለው መንገድ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሂደቶችን በአስቸኳይ መልስ
ለመስጠት ሁሉንም ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላት ያለውን ፍላጎት ሊታመን በሚችል ሁናቴ ፍቃደኛ መሆኑን በተግባር
እንዲያሳይ ነው። ለዚህም ዓይነት ሂደት ያለ ምንም ወገንተኛነትና አድልዎ በሌለበት ለማመቻቸት ራሳችንን
እንደምንሰጥ የምንገልፀው በሙሉ ቁርጠኝነት ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው የሽምግልና ስራችንን ለመስራት
መኖሪያውን አዲስ አበባ ካደረገው የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች ድርጅት ጋር የድርጅቶቹ ድርጅታዊ ሕልውና
እኩልነትና ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፥ አብሮ ለመስራት ያለንን ፍላጎትና ዝግጁነት ለመግለፅ እንወዳለን። የዚህም
ድርጅት ዓላማው “በሀገራችን ዴሞክራሲ የሰፈነበት፣ የሰብዓዊ መብቶችና በጎ ስነ ምግባር የተከበረበት፣ ብልፅግና
የተስፋፋበት እና አንድነቱ የፀና ህብረተሰን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የመከባበር፣ የመደጋገፍ፣ የዕርቅና
የይቅር ባይነት ሰላማዊ ባህል ስር እንዲሰድ” ስሆን ይህም ከእኛ አስተሳሰብና አሰራር ጋር የሚገጥም ሆኖ ስላገኘነው
አብረን መስራት ከጀመርን ጥቂት ጊዚያቶች አልፏል።
ሁለተኛው የዚህ ግልፅ ደብዳቤያችን ዓላማ ሁሉም የኢትዮጵያ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ትብብርና አንድ
ወጥ መድረክ(platform) መፍጠር አማራጭ የሌለው ታሪካዊ ግዴታ እንዳለባቸው ለማስታወስና በአስቸኳይ
የትብብር ሂደት እንዲጀምሩ ለማበረታት ነው። አሁን የተፈጠረውን የሕዝብ እንቢተኝነት የአማራጭ ሃይሎች
ለማስተባበርና ከመንግስት ጋር ለመወያየት ዝግጁ ሆኖ አለመገኘት ታላቅ የፖለቲካ ድክመት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ
ነው። ይህንን ክፍተት በጊዜው መፍትሔ ካልተገኘለት የፖለቲካ መሪ አልባነት የሚያስከትለውን አደጋ መገመት ብዙ
ትንተናና ዘገባ የሚያስፈልገው አይመስለንም። ስለሆነም ሁሉም ዲሞክራሲያዊ አማራጭ ሃይሎች በአስቸኳይ
ልዩነታቸውን በውይይትና በመግባባት አጥበው ራሳቸውን ለሰላሙ ጉዞ ማዘጋጀትና መደራጀት ታሪካዊ ግዴታቸው ነው
ብለን እናምናለን። የተሳካ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የተበታተነውን የአማራጭ ሀይሎችን አስተሳሰብ በውይይትና
በመግባባት ድልድይ ስርተው አንድ ወጥ በሆነ መልኩ ከመንግስት ጋር ለመወያየትና ለመደራደር አቅም በማዳበር
መሆኑን መገንዘብና ይህንን ሂደት በአፋጣኝ መጀመር እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝነት ያለው ጥያቄ ነው። እኛም
ለዚህ ውይይት ማመቻቸትና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁዎች ነን።
ለማጠቃለል እኛ የተደራጀነው በአሜሪካ አገር ቢሆንም በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ዲሞክራሲን፥ ሰላምን፥
ህብረትን፥ እኩልነትን፥ የሕግ የበላይነትና እድገትን ለማምጣት ከሚጥሩ ጋራ አብረን ለመስራት ፍቃደኝነታችንን
በደስታ እንገልፃለን።
መልካም የሰላም የትብብርነት የእኩልነት ልዩነታችን ጉልበታችን አንድነታችን የሚሆንበት አዲስ ዓመት
ይሁንልን!
በድርጅቱ ስም፥
ብርሃኑ መንግስቱ
ጷግሜ 5/2008
Leave a Comment