1
ሚያዝያ 30 ፣ 2010 ዓ.ም.
ለክቡር ዶ/ር ዓብይ አሕመድ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚንስቴር
ጉዳዩ፡ ክቡርነትዎ ያቀረቡትን የሰላምና ዕርቅ ራዕይ እንዲተገብሩ ስለማበረታታት እና ራዕዩን ለመተግበር
የወደፊት ትብብርና ድጋፍ ስለ ማቅረብ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአሳሳቢ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀዉስ ዉሰጥ
በመግባትዋ ሁላችንም ስጋት ገብቶን እንደ ነበር ግልጽ ነዉ። ሆኖም ክቡርነትዎ ሀገር ለማዳንና
ህዝባችንን ካንዣበበበት ሁለንተናዊ አደጋ ለመታደግ ብሎም ሰላም፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ብልጽግና
የሰፈነባትን ፤ ሁላችንም እንደ ዜጎች ተከባብረንና ተቻችለን ሰብዓዊ መብታችን ተከብሮ የምንኖርባትን
ኢትዮጵያ ለመገንባት በድፍረትና በግልጽነት እርሶ በጀመሩት እንቅስቃሴ ሀገራችን ከመቼዉም በበለጠ
የተስፋ ጮራ ፈንጥቆባታል ብለን በጽኑ እናምናልን።
በየትኛዉም አመክንዮ ፡ ሀሳብ ንግግርን፣ ንግግርም ተግባርን ስለሚቀድም ክቡርነትዎ እንደ ሀገር
መሪ ያደረጓቸዉን ንግግሮች በትልቅ አክብሮትና አድናቆት የምንቀበል መሆናችንን እየገለጽን፤ እኛ በዚህ
ደብዳቤ ግርጌ ስማችንን የዘረዘርን በዉጭ ሀገር የሚንኖር በሰላም፣ በዕርቅ፣ በመግባባትና በሰብዓዊ
መብቶች ዙሪያ ስንሰራ የቆየን ግለሰቦች የክቡርነትዎን ራዕይ በተቻለን ሁሉ ለማገዝ፤ እንዲሁም በአግባቡ
እንዲተገበሩ ለማበረታታትና ለመደገፍ የምንፈልግ መሆናችንን በታላቅ ደስታ ልናሳዉቆት እንወዳለን።
ከዚህ አንጻር እርስዎ በፓርላማ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር ዉስጥ ካነሷቸዉና እንዲሁም
ከዓላማችንና ከዚህ ደብዳቤ ርዕስ ጋር ተጓደኝነት ያለቸዉ ሀሰቦች ከብዙ በጥቂቱ ለማስታወስ ያህል፦
ስለ ዕርቅ፦ «መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው!» «በአገር ውስጥም ሆነ
በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር
ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ
እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ።»
ስለ ሰላም፦ «ለሰላም መሰረቱ ፍትህ ነው። ሰላም የግጭት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም
በመግባባት ላይ የተመሰረተ ጽኑ አንድነታችን ነው፣ ሰላም- መተማመናችን ነው። ሰላም-በሁላችንም
ፈቃድ ዛሬም የቀጠለ የአብሮነት ጉዞችን ነው። ሰላም አለመግባባትና ተቀርኖዎችን በሰለጠነ መንገድ
መፍታት የሚያስችል መንገድና ግባችን ነው።»
ስለ ዜጎች መብት፦ «በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነጻነትና ፍትህ እንዲሰፍን፣ የሕግ
የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን።»
ስለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፦ «ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደ
ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደ
መጣ አገሩን እንደ ሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው።»
ክቡርነትዎ እንደ ሚገነዘቡትና በተለያዩ ጊዜያትም እንደጠቀሱት እነዚህ ተስፋ ፈንጣቂ ሀሳቦችዎ
ሁላችን ተጋግዘን የየድርሻችንን ካልተወጣን በቀር ዕዉን ሊሆኑ አይችሉም። ይህን በርስዎ በኩል
የተጀመረዉን መልካም ሀሳብ ከማሳከት ረገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይረባረባል ብለን ተስፋ እያደረግን
ጉዞዉ ግን ቀላል እንደ ማይሆንም እንገነዘባለን።
ከግርጌ ስማችንን ያሰፈርን በዲያስፕራ የምንኖርና ስለ ሰላም፣ ዕርቅ ፣ ሀገራዊ መግባባትና ሰብዓዊ
መብቶች የምንቆረቆር ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች
የልዩነት ትርክቶችን አፍርሰው ሰላም፣ ዕርቅና ፍትህን ማረጋገጥ የሚችሉባቸውን ትርክቶች ፣ መድረኮች
፣ መዋቅሮችና አገናኝ ማህበራዊ ሃብት (Bridging Social Capital) መፍጠርና ማበረታታት
ያስፈልጋል ብለን እናምናለን።
ዘላቂ ሰላም በሃገራችን እንዲኖር ሁከትና ብጥብጥን ከማቆም ያለፈ፤ የእልቂት ዑደትን የሚያቋርጥ
እንዲሁም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ መዋቅራዊ ሁከቶችን (Structural Violence) ለማስቀረት
የሚያስችል የሰላም ስራን በአስቸኳይ መጀመር እንደ ሚያስፈልግ እናምናለን። ክቡርነትዎ ለሃገራችን
ዘላቂ የግጭት መፍትሄዎችን ለማምጣት ያለዎትን እቅድ በተቻለ ፍጥነት እንዲቀርጹና ለህዝብ
እንዲያሳውቁ ፤ እንዲሁም ወደ ተግባር እንዲለውጡ በአክብሮት ጥሪ እያስተላለፍን የሰላምና ዕርቅ
ስራዎን ለማበረታታትና የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
“ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
ፈራሚዎች
(Endorsers)
1. ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና
ዩናይትድ ስቴትስ
2. ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ዩናይትድ ስቴትስ
3. ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል
ዩናይትድ ስቴትስ
4. አቶ ሽመልስ ወርቅነህ
ዩናይትድ ስቴትስ
5. ዶ/ር አባድር ኢብራሂም
ዩናይትድ ስቴትስ
6. አቶ ኦባንግ ሜቶ
ካናዳ
7. አቶ ጳውሎስ አበበ
ስዊድን
8. አቶ ያዬ አበበ
ዩናይትድ ስቴትስ
9. ዶ/ር ገበየሁ እጂጉ
ዩናይትድ ስቴትስ
10. ፕ/ሮ ብርሃኑ መንግስቱ
ዩናይትድ ስቴትስ
11. ወ/ሮ አስቴር አስገዶም
ስዊድን
12. ዶ/ር ኡስማኤል ቋዳህ
ዩናይትድ ስቴትስ
13. አቶ ግደይ ዘራጽዮን
ኖርዌይ
14. አቶ ግርማ ሞገስ
ዩናይትድ ስቴትስ
15. አቶ ዮናስ መብራቱ
ጀርመን
16. ዶ/ር ብርሃኑ ለንጂሶ
ዩናይትድ ስቴትስ
17. አቶ ተክለሚካኤል አበበ
ካናዳ
18. ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ
ዩናይትድ ስቴትስ
19. አቶ ነጋሲ በየነ
ዩናይትድ ስቴትስ
20. ዶ/ር ሰይድ ሀሰን
ዩናይትድ ስቴትስ
21. ወ/ሮ ለምለም ጸጋው
ዩናይትድ ስቴትስ
22. አቶ አቤል ጋሼ
ዩናይትድ ስቴትስ
ማስታወሻ፦ ይህ ደብዳቤ መነሻ ደብዳቤ ነው። ተጨማሪ ዝርዝር የተግባር ሀሳቦችን በሌሎች ደብዳቤዎች ላይ
እናቀርባለን። – ከአክብሮት ጋር።
Leave a Comment