የዐማራው ሕዝብ ህይወትና ደህንነት ዘውግ ተኮሩን ስርዓት ከመቀየር ጋር አብሮ የሚሄድ ጉዳይ ነው
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
የእርስ በእርስ ጦርነት ዛሬ አልተጀመረም።
የወልቃይት ጠገዴ፤ የጠለምት፤ የዋልድባ፤ የሰቲት ሁመራ፤ የራያና አዜቦ፤ የትግራይ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ። ሊወገድ የሚችል ጦርነት መካሄዱ አሳፍሮኛል። ሊካድ የማይችለው ሃቅ ግን የዐማራው ሕዝብ በሽብርተኛው ብድህወሓትና በኦነግ ሽኔ ተከታታይ እልቂት ሲካሄድበት ቆይቷል። ህወሓት ባወጣው ማኒፌስቶ (መመሪያ) የፋሽስቱን የጣልያን ግፍ፤ በደልና የበላይነት ተመሳሳይ ነው በማለት “የዐማራው ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ዋናው ጠላት ነው” ብሎ ፈርዶበታል። ይህንን ትርክት ሌሎች የብሄር ጽንፈኞችና እንደ ኦነግ ሽኔ ያሉ ሽብርተኞች መሳሪያ አድርገው ዐማራውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዩን ጨፍጭፈውበታል። ይፋ አይሁን እንጅ ዐማራውን ኢላማ ያደረገ ያልታወጀ ጦርነት ሲካሄድ ከአርባ ዓመታት በላይ ሆኖታል።
ህወሓት የቀሰቀሰውን ጦርነት ጀግናው የመከላከያ ኃይል፤ ከነዋሪው ገበሬ፤ ከፋኖው፤ ከሚሊሺያውና ከሌላው አጋር ኃይል ጋር ሆኖ የሚያካሂደውን የጸረ- አመጸኞች ወይንም ሽብርተኞች፤ በተለይ ጸረ-ሰላም፤ እርጋታና ጸረ-ከሃዲነት እንቅስቃሴ አደንቃለሁ።
ይህ አላስፈላጊ ጦርነት የተጀመረው በህወሓት፤ በኦነግ ሽኔ፤ በጅሃዲስቶችና ከጀርባ ከፍተኛ ድጋፍ በሚሰጡ ኃይሎች፤ በተለይ በግብፅ መሆኑን በተከታታይ ትንተናዎቸ አሳስቤ ነበር። ኢትዮጵያን እኛ ካልገዛናትና ካልመዘበርናት የደም መሬት አድርገናት ትበተን የሚሉት ህወሓትና አጋሩ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ወታደራዊ ኃይል (The Oromo Liberation Army/OLA) ያመጡት ጠንቅ ነው።
ወረተኛ ካልሆንን በስተቀር ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና እርጋታ ያገኘው መቸ ነው? እኔ ወጣት ከአባቴ ጋር በበቁሎው ተሳፍሬ፤ እንዳልወድቅ ወገቡን ይዠ በያካባቢው ለሰርግ፤ ለለቅሶ፤ ለልዩ ልዩ በዓል ስንዞር አንድ ሰው ሌላውን “በሕግ አምላክ” ሲለው ካለበት የማይንቀሳቀስባት አገር ነበረች–እትዮጵያ።
የደርግ መንግሥት “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ብሎ ሕዝቡን ከቀሰቀሰ በኋላ የሆነውን የእኔ ትውልድ ያስታውሰዋል።
ሻቢያ፤ ህወሓትና ኦነግ የነጻ አውጭ ድርጅቶች ሆነው ደርግን ሲያስወግዱና ለሥልጣን ሲደራደሩ አብሮ የተወገደው ኢትዮጵያዊነት ነው። የገነነው ደግሞ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጽንፈኝነት፤ አመጸኝነት፤ ነፍስ-ገዳይነት፤ በተራው ሕዝብ ስም ድርጅታዊ መዝባሪነት፤ የዘውግ ተረኛነት ወዘተ ነው። በሰላም፤ በፍትህ፤ በሕግ የበላይነት የሚያምኑትን ፕሮፌሰር አስራትን የገደለ ስርዓት ነው የተመሰረተው። ከሳቸው በፊት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ፤ ግፍና በደል ችላ ብንለው እንኳን ከሳቸው በኋላ የተፈጸመውን ብንመረምረው መረጃው ብቻ አንዲት መጽሃፍት ቤት ይሞላል።
እኔ ዓለም ባንክ ሆኘ ህወሓት የሚያደርገውን ግፍና በደል በኢትዮሜድያና በኢትዮጵያን ሪቪው “እውነቱ ከፍያለው” በሚል በብእር ስም ጭምር እተች ነበር። ህወሓቶች ጭፍጨፋ ሲያካሂዱ መረጃ ሳይተው ነበር (They were silent murderers). የዓለምን ሕዝብ ያታለሉት በመለስ ዜናዊ አማካይነት እንደ ነበር አንርሳ። ዓለም ባንክ፤ አይ ኤም ኤፍ፤ የአሜሪካ፤ የእንግሊዝና ሌሎች መንግስታት ይህን ጨካኝ ሰው ከሩዋንዳው ካጋሚ ጋር የአፍሪካ “ትንሳኤ መሪዎች (Africa’s Renaissance men)” ብለው ሸልመውት ነበር።
ህወሓት ጨካኝ፤ ዘራፊ፤ ጸረ-ሰላም፤ ጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይል ሆኖ የሚሰራ ድርጅት ነው። ህወሓትና ሌሎች ጽንፈኛና ሽብርተኛ ቡድኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ደህንነት፤ የአገራችንን ሰላም፤ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት አይደግፉም። ኢትዮጵያ ከጠፋች ደግሞ ዲሞክራሲ፤ ልማት ወዘተ ቀልድና የፖለቲካ ንግድ ነው።
ህወሓትና የዘረጋው የጥፋት መዋቅር መፍረስ አለበት። በተመሳሳይ፤ ህወሓት የፈለፈላቸውና ያሰለጠናቸው የሽብር ምሽጎች መፍረስ አለባቸው። ኦነግ ሽኔ ሌላው መፍረስ ያለበት ድርጅት ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ የተካሄደውን አስቡት። ህወሓት የዘርፈውን ይዞ መቀሌ መሸገ። ከመሸገ በኋላ በተከታታይ ያካሄደው እልቂትን ነው። የውክልና ጦርነት አካሂዷል። እያካሄደ ነው። ወርቃማ የሆኑት እነ ዶር አምባቸው መኮነን መስዋእት ሆነዋል። ከጀርባ ሆኖ የእንሱን እልቂት፤ በተከታታይ የዐማራውንና የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን እልቂት ያካሄደው ሽብርተኛ ኃይል ህወሓት ነው።
ህወሓትና ኦነግ ሽኔ ሲፈራርሱ አብሮ የሚፈርሰው ሽብርተኝነት ነው። በወለጋ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በጉራ ፈርዳና በሌሎች አካባቢዎች ዐማራውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ኢላማ ያደረጉ ኃይሎች ሁሉ ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለባቸው። በተጨማሪ፤ ለእልቂት መሰረት የሆኑት ተቋማት መለወጥ አለባቸው (The root causes {institutional and structural} must be overhauled).
Leave a Comment