ሴቶች ቅራኔዎች በመፍታት ሂደት ላይ ያላቸው ሚና

“ያለሴቶች ተሳትፎ ዴሞክራሲ የማይቻል ነው። እድገትም ያለዴሞክራሲ የማይታሰብ ነው።”  ማደሊን ኬ አልብራይት

በራዕይ ኢትዮጵያ ፯ኛ  ጉባዔ ላይ አዲስ አበባ የቀርበ

ታህሣሥ 18 ቀን 2011/ December 27, 2018

በወሰንየለሽ ደበላ

መነሻ ሀሳብ  

        ለአንድ አገር ብልፅግና የሀገሪቱ መረጋጋትና ሰላም መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ሰላም ማለት ስጋትና ፍርሃት የሌለበት፣ ጦርነት የማይካሄድበት፣ ግጭትና ሁከት የማይፈጠርበት፣ አለመረጋጋት፣ ጭቆና፣ ማስፈራራት፣ ጥቃት፣ ስድብ፣ አድልዎ የሌለበት ማለት ነው። ሰላም ምንም እንኳን የአመፅ አለመኖር ቢሆንም አወንታዊ ሰላም ግን በሰላማዊ ህዝቦች የሚንጸባርቅና ዘላቂ የሆኑትን ዝናባሌዎችን፣ መዋቅሮችንና ተቋሞች የሚገለፁበት ነው።  የሰላም ድባብ መኖር ለእድገትና ለልማት አስፈላጊ መሠረት ነው። በለውጥ ላይ ያለ ሀገር የመጀመሪያ እንቅፋት የሚሆንበት የሰላም መደፍረስ ነው።

        ሰላም ሲደፈርስ ገበሬ አርሶ መብላት፣ ነጋዴ ነግዶ መግባት፣ ልጆች ተጫውተው፣ ወጣቶች ተምረው፣ ከብቶች ተሰማርተው በሰላም መግባት አይችሉም። ማሕበረሰቡ በሰላም ወጥቶ ካልገባ ሀገር በህውከት ውስጥ ካለ መንግሥት ተረጋግቶ ሀገሪቱን ማስተዳደር አይችልም። ሰላም ከሌለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ የፖለቲካ መረጋጋትና የማህበራዊ ብልፅግና የማይታሰቡ ናቸው። ሰላም ከሌለ ሕዝብ ለከፋ ድህነትና በሽታ የተጋለጠ  ይሆናሉ። ለምሳሌ እንደ ኤድስ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ በመራባት ትውልድን እምሽክ ያረጋሉ።

        አንድ አገር ከነበረበት የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ለመውጣትና  ወደ ተሻለ የማህበርሰብ ዕድገት፣ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲዊ  አስተዳደር ለመሸጋገር በሚያደርገው ጥረት ቀድሞ በሥራ ላይ የነበረው አስተዳደር የዘራው አሉታዊ አስተሳሰቦች፣ ፍርሃት፣ አለመተማመን፣ ስጋትና ድህነት ምክንያት  በየቦታው የተጫሩት ግጭቶች  እንቀፋት ሰለሚሆኑ የለውጡን  ሂደት ይፈታተኑታል።

        በተለይ ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት በሥልጣን ኮርቻ ላይ የተንሰራፋው አስተዳደር ያከናወናቸው የአስተዳደር ብልሹነት፣ አምባገነናዊ አገዛዝ፣ ሙስና፣ እኩይ ተግባሮች፣ ለህውከትና ግጭቶች የተመቻቹ ሁኔታዎች ፣ እርስ በርስ የሚያጋጩና የሚያባብሱ ቅራኔዎች የሀገሪቱን ሰላም ማደፍረሳቸው እያየነው ያለ ሀቅ ነው። እንዲህ ዓይነት የሰላም መደፍረስ ቀደም ብሎ ለውጥ የተካሄደባቸው የተለያዩ ሀገሮች ላይ የታየ ችግር ነው። ስለዚህ በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች እየተካሄዱ ያሉት የግጭት ቀውሶች ምክንያት የደፈረሰውን ሰላም ለማረጋጋትና የለውጡን ሂደት እንዳይጨናገፍና የፈነጠቀው ለጋ የተስፋብርሃን እንዳይደበዝዝ የዴሞክራቲክ ኃይሎች በሙሉ በንቃት በሰላም ግንባታ ላይ መሳተፍ አለባቸው። ማህበረሰቡን የሚያሳተፉ የተለያዩ ሕዝባዊ ተቋማት ማደራጀት፣ የሰላም ጉባኤዎችን ማካሄድ፣ የማህበረሰቡን አመለካከትና አስተሳሰብ ለመቀየር የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ሕዝቡን በመረጃ በማስታጠቅ የአስተሳሰብና የአመለካከት አድማሱን እንዲሰፋና እንዲበሰል በማድረግ ለሰላም ውይይቶች ማዘጋጀት ያስፈልጋል። እንደ አሸን መፍላት ካለባቸው ሕዝባዊ ተቋማት መካከል ግማሹንና ከዛም በላይ የሆነውን የማህበረስብ አካል የሚወክለው የሴቶች ሕዝባዊ ማህበራት  አንዱ ነው።

          ለረጅም ዓመታት በጎሣ ፣ በቋንቋ፣ በመሬትና በተለያዩ ምክንያቶች የተጋጨ፣ ቂምን  ያዘለ ማህበረሰብ ከጉዳቱና ከቂሙ እንዲያገግም የተለያዩ ማህበራዊ ጥረቶች መካሄድ ይኖርባቸዋል። ህዝቡ ላይ የደረሱትን ጉዳቶችና ግጭቶች፣ የአካልና የመንፈስ ስብራቶች እውነትን መሠረት በአደረጉ፣ ፍትህን ተግባራዊ በሚያደርጉ መልካም አስተሳሰብ፣ በቅን ልቦና በበጎ አንደበት መጽናናትና መታከም አለባቸው። ህዝቦች እርስ በርሳቸው በመነጋገር፣ በመወያየትና በመጽናናት ሀዘናችውን በጋራ በመወጣት ችግራቸውን በይቅርታና በሰላም ለመቋጨት መስማማት አለባቸው። ወደ ሰላም ለመምጣት በሚደረገው ጥረቶች ውስጥ ሁሉ  የሴቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሴቶችን እንዲሳተፉ ማበረታታት ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባዋል። የሴቶች መሳተፍ ውጤቱንም የተሳካና አወንታዊ ያደርገዋል። ሴቶች መሳተፋቸው ሌላው ጥቅሙ የተለያዩ የማህበረሰቡ አካሎችን በሰላም  የውይይት ሂደት ላይ እንዲሳተፉ ዕድል ይሰጣል። ሴቶች ሲሳተፉበት አብዛኛው የማህበረሰቡ አካሎች እስከ ታችኛው ያለውን ነዋሪ ወጣቱን ጨምሮ በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ለማሳተፍ ያስችላል። ጉዳይ የጋራ ችግር መሆኑን ለመገንዘብና የሚገኘውም ውጤት የጋራ ጥቅም መሆኑን ለማስረዳት ቀላል ይሆናል። እንዲሁም ሴቶች በመሳተፋቸውና እይታቸው በመካተቱ ውይይቱን ልዩ መልክ ከመስጠቱም በላይ የባለቤትነት ስሜት ስለሚፈጥርባቸውም የሚገኘውን ሰላም ይከባከቡታል። ሴቶች በመሳተፋቸው ሌላው የሚገኘው ጥቅም ማህበረሰቡ ለሴቶች ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ለመቀየር መጠነኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

To Read More Please Click Here

Share: